13/02/2018
ባልተገባ መልኩ የተያዙ የመንግሥት ቤቶችን የማስለቀቅ ስራ እንደሚጀመር የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ገለፀ
**************
ሀዋሳ፣ ጥቅምት 13፣ 2018 (ኤስቢሲ) ባልተገባ መልኩ የተያዙ የመንግሥት ቤቶችን የማስለቀቅ ስራ እንደሚጀመር የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ገልጿል።
የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ አቶ ተክሌ ጆምባ እንደገለፁት በተለያዩ አጋጣሚዎች በከተማዋ የሚገኙ የመንግሥት ቤቶች የመንግሥት ቤት ወደማይገባቸው ግለሰቦች መዘዋወሩን በማስታወስ በተለይም የግል ቤት ኖሮአቸው በመንግሥት ቤት የሚኖሩ ግለሰቦችን ቤት በመረከብ ለሚገባቸው የከተማዋ ነዋሪዎች ለማስተላለፍ ዝግጅት መደረጉንም አመላክተዋል ።
የክልሉ መንግሥት ይህ ተፈፃሚ እንዲሆን አቅጣጫ አስቀምጧል ያሉት ከንቲባው የከተማው አስተዳደርም ለተፈፃሚነቱ በቁርጠኝነት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል ።
በከተማዋ ያለውን የመኖሪያ ቤት አቅርቦት ችግር ለማቃለል መንግስት ይሰራል ያሉት አቶ ተክሌ በተለይም ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ዜጎች ትኩረት ያደረጉ ፕሮጀክቶችን ወደ መሬት ለማውረድ ዕቅድ መዘጋጀቱን አመልክተዋል ።
አዳዲስ የቤት አማራጭ ዕድሎችን ከመፍጠር በተጓዳኝ ከዚህ በፊት ተጀምረው የነበሩ የቤት ግንባታዎችን በማጠናቀቅ ለተጠቃሚዎች ለማስተላለፍ የከተማ አስተዳደሩ እየሰራ ነው ብለዋል።
በጀማል የሱፍ
ለሀሳብ ልዕልና
ቀጣዮቹን ማስፈንጠሪያዎች በመጫን የኤስቢሲ ቤተሰብ ይሁኑ!: -